በዓለ ጥምቀት – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

በዓለ ጥምቀት

            ሸክላ ሰውነታችን
ድኅረ ተሰብረ አጽንዖ ለሰብእናነ ልሕኵት፣
ለብሐዊ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት።
ትርጉም፦
ሸክላ ሰውነታችን ከተሰበረ በኋላ
ጥበበኛ/ሸክላ ሠሪ ክርስቶስ በአዲስ ውኃ ጥምቀት መልሶ አጸናው (መልሶ አደሰው)።
ይህ የቀደምት አባቶቻችን ቅኔ የሚያስረዳን ነገር አለው።
✔️እንደሚታወቀው ሸክላ ሠሪ ሸክላዋን ከሠራች በኋላ ነቅ ብታገኝበት ወይም ቢሠበርባት ታፈርሰውና እንደገና በውኃ አርሳ መልሳ አዲስ አድርጋ ትሠራዋለች። ሸክላውም ከፊተኛው ይልቅ የጸና እና ቶሎ የማይሰበር ይሆናል።
☑️በዚህ አንፃር ባለቅኔው የገለጡት
የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጣሱና አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ከእግዚአብሔር ተለየ ፣ ጸጋውን ተገፈፈ፣ ልጅነቱን አስወሰደ በዚህም ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈረደበት። ስለሆነም ሰውታችን እንደሸክላው በኃጢአት ፈረሰ ጎሰቆለ ከክብር ተራቆተ ከፈጣሪው ጋር ያለው ግንኙነት ተቋረጠ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ብዙ ክብር አጣ። ኃጢአት “ኃጥአ – አጣ” ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን ማጣት የሚል ትርጉም ይሰጠናልና ። ያጣነው ምንድነው? ከተባለ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የሚያደርገንን ልጅነታችንን አጣን፣ ገነትን ያህል ቦታ ተነጠቅን፣ ጸጋችንን አስወሰድን፣ በገዛ ፈቃዳችንም ” አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ = አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ ነው ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት” ብለን በመፈረም እራሳችንን ከእግዚአብሔር አገልጋይነት ወደ ዲያብሎስ አገልጋይነት አሸጋገርን። ዲያብሎስም ለሰው የማያዝን ጽኑ ጨካኝ ነውና በእግረ አጋንንት እንድንጠቀጠቅ አደረገን በጨለማ እስር ቤት ውስጥ አሠረን። እንዲህ አድርጎ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን አስጨንቆ ገዛን በዚያ የጭንቀት ዘመን ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ በሞት ጥላ ሥር ሁነው አበው ሲያለቅሱ ነቢያት ስለድኅነታችን ትንቢት ሲተነብዩ ሱባኤ ሲቆጥሩ ሰውን ሲያስተምሩ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ሲያደርጉ ኑረዋል። “ቀን ቢደርስ አባ ይፈርስ” እንዲሉ የቀጠሮው ቀን ቢደርስ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእናታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነቢዩ አስቀድሞ በትንቢት ” ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ፯፥ ፲፬) ብሎ እንደ ተናገረ በድንግልና ተጸንሶ በድንግልና ተወለደ። “አሐዱ ዘእምቅድስት ሥላሴ ርእዮ ትሕትናነ አጽነነ ሰማየ ሰማያት መጽአ ወኀደረ ውስተ ከርሠ ድንግል ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ ወተወልደ በቤተልሔም በከመ ሰበኩ ነቢያት አድኃነነ ወቤዘወነ ወረሰየነ ሕዝበ ዚአሁ = ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብለው ከሚመሰገኑ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ በመንጸፈ ደይን መውደቃችንን በእግረ አጋንንት መጠቅጠቃችንን አይቶ ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ከቅድስት ድንግል ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆነ። ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው እንዳስተማሩ በቤተልሔም ተወለደ። ፈጽሞ አዳነን፤ በሐዲስ ተፈጥሮ በጥተ ተፈጥሮ ወገኖቹ አደረገን” እንዳለ (ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም)
እንደሰው ግእዘ ሕፃናትን እየፈጸመ አደገ። ግእዘ ሕፃናት ማለትም በእየጥቂቱ ማደግ ነው። ” ልህቀ በበሕቅ እንዘ ይትኤዘዝ ለአዝማዲሁ እንተ ይእቲ እሙ = ለዘመዶቹ እየታዘዘ በእየጥቂቱ አደገ ይህቺውም እናቱ ናት” እንዲል (ሉቃ፪፥፶፩)። በሠላሳ ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ ተጠመቀ። በመጠመቁም ከኃጢአት የምታነጻ፣ ልጅነታችንን የምታስመልስ ፣ ከእግዚአብሔር ጋራ አንድ የምታደርግ ፣ ሊቁ በቅኔው እንደገለጡት በኃጢአት የፈረሰው ሸክላ ሰውነታችን የሚታደስባት ጥምቀትን መሠረተልን። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ” ወለደነ በጥምቀቱ ለቅድስት ቤተክርስቲያን = የቤተክርስቲያን ልጆች እንሆን ዘንድ በጥምቀት ወለደን” እንዲል (በመዋሥዕት መጽሐፉ )
የቅኔውም ሰምና ወርቅ የሚያስረዳን ሸክላ ሠሪዋ የሠራችው ሸክላ ሲሰበርባት ሲፈርስባት መልሳ ከስክሳ በውኃ አርሳ አድሳ እንደምትሠራው ሁሉ፤ ጥበቡ የባሕርዩ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከአፈር ፈጥሮ አዋቂ ፣ ተናጋሪ እና ሕያዊት የሆች ነፍስን ፈጥሮ አዋሕዶ ልጅነትን አሳድሮ በመንፈስ ቅዱስ አክብሮ በገነት አኖረው። ( የነፍስና የሥጋ ተፈጥሮ በአንዴ እንደሆነ ልብ እንበል ለያይተን ስንናገር በተለያየ ሰዓት እንዳይመስለን)
በኋላ ትእዛዙን ቢያፈርስ ከገነት አባረረው ሸክላው እንደሚፈርስ በኃጢአት ተያዘ፣ ሸክላው በውኃ ታድሶ እንደገና እንደሚሠራ መድኃኔዓለም በጥምቀት ልጅነትን እንዲያገኝ በጥምቀት እንዲድን ማድረጉን ነው የሚያስረዳን።
የፈረሰው ሸክላ ተመልሶ ሸክላ መሆን የሚችለው በውኃ ነው። እኛም ልጅነትን የምናገኘው ከኃጢአት ነጽተን ድኅነትን የምናገኘው በጥምቀት ነው። ያለ ጥምቀት ልጅነት፣ ያለ ጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ፣ ያለ ጥምቀት ድኅነት ፣ ያለ ጥምቀት መንግሥተ ሰማያት መግባት ፣ ያለ ጥምቀት ዲያብሎስን ማራቅ በፍጹም አይቻልም ቅዱስ መጽሐፍም ” ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወዘኢተጠምቀ ይደየን = ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል” (ማር፲፮፥፲፮)።
” ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እያመናችሁ ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” ሐዋ፪፥፳፰) እንዲል።
✅ ስለጌታችን ጥምቀት፦ የት ተጠመቀ ? በማን ተጠመቀ ? ለምን ተጠመቀ? ጥምቀቱን ለምን በሠላሳ ዓመቱ አደረገው? ለምንስ በውኃ ተጠመቀ? ለምን በዮርዳኖስ ተጠመቀ? በደም በወተት ለምን አልተጠመቀም? በጥምቀቱ ምን አገኘን? ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች የቻላችሁ መመለስ ትችላላችሁ ወይም ብዙ ጸሐፍት እየጻፉ ስለሆነ መልካም የሆነውን አንብባችሁ እንድትጠቀሙ በዕለቱም በእየባሕረ ጥምቀቱ ተገኝታችሁ እንድትማሩ እየጋበዝኩ መደጋገም እንዳይሆን እና እንዳያሰለች ከዚህ አልፈዋለሁ። ዋና ሐሳቤ በጥምቀት ድኅነት እንደሚገኝ ያለ ጥምቀት ግን መዳን እንደሌለ ለመግለጥ እና የቀደምት አባቶቻችን በቅኔ ነገረ ድኅነትን እንዴት ይገልጡት እንደነበር ለማሳወቅ ነው።
የዓመት ሰው ይበለን ከበዓለ ጥምቀቱ በረከት ይክፈለን!!! አሜን!
መምህር ዳንኤል አለባቸው የሐዲስ ኪዳን መምህር
ጥር፲/፳፻፲፫
Share this

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *