በጎ አድራጎት – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

ቤዛ ብዙኃን ምግባረ ሠናይ በጎ አድራጎት ማኅበሩ ራዕይና ተልዕኮ

ራዕይ፡- የተጎዱና የተቸገሩ ወገኖቻችን ሕይወታቸው ተለውጦና ተሻሽሎ ሲደሰቱ ማየት፡፡

ተልኮ፡- ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከልና ሕመምተኞችን በመደገፍ እርስ በእርስ እንዲረዳዱ ጥረት ማድረግ፡፡

እሴት፡- ከጎጂ ልምዶችና አጉል ሱሶች መጠመድን በማስወገድ ድኅነትን በሥራ ማሸነፍ፡፡

ዓላማ፡-

  1. በቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን አረጋውያንን በየቤታቸው መንከባከብና የሚያስፈል ጋቸውን ድጋፍ ማድረግ፤
  2. እናት አባት የሞተባቸውን ሕፃናት በስነ ምግባር ታንጸው የዘመናዊ ትምህርታቸውን እንዲማሩ የትምህርት ቤት ማቴሪያል ሙሉ ድጋፍ በማድረግ ማስተማር እና ለውጤት ሲበቁ ማስመረቅ፤
  3. በዓመት አንድ ጊዜ ለሕፃናቱ የልብስና የጫማ ድጋፍ ማድረግ፤
  4. በተለያዩ ሱስ ተይዘው የተቸገሩ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን በምክርና በትምህርት በመመለስ በሙያ አሰልጥኖ እራሳቸውን ማስቻል፤
  5. የሥራ ፈጠራን በማበረታታትና በማጎልበት ድጋፍ መስጠት፤
  6. ከሌሎች መሰል አጋር ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት፤
  7. ኤች አይቪ በሽታን መከላከልና በበሽታው የተያዙትን መደገፍ ይሆናል፡፡

 

የቤዛ ብዙኃን ምግባረ ሠናይ የበጎ አድራጎት ማኅበር የሚሰራውን ሥራ በተመለከተ

በአልጋ ላይ የዋሉ የአልጋ ቁራኛ ሕመምተኞችን መርዳት

በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዘው በአልጋ ላይ የሚገኙ ሃምሳ /50/ የአልጋ ቁራኛ ሕመምተኞችን በቤት ለቤት ድጋፍና እንክብካቤ በማድረግ መርዳት፡፡

እናት አባት ለሞተባቸው ሕፃናት ድጋፍ መስጠትን በተመለከተ

አንድ መቶ ሃምሳ /150/ የሚደርሱ እናት አባት የሞተባቸውን ሕፃናት የትምህርት ቤት ድጋፍ በማድረግ ማስተማር እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር እንዲኖራቸው ማስተማር፡፡ መዝ. 60 ቁ.1

ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከል የሚደረግ ድጋፍ በተመለከተ

ኤች አይቪ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ዙሪያ ማስተማርና በቫይረሱ ለተያዙት ህመምተኞች ድጋፍ በማድረግ ማጽናናት፡፡ እንዲሁም ወጣቶችን ከሱሰኝነት በማላቀቅ አሰልጥኖ እራሳቸውን ማስቻል ይሆናል፡፡

የነዳያን ግብዣን በተመለከተ

ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስብ ምስጉን ነው፤ እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል፤ እግዚአብሔር ይጠብቀዋል ህያውም ያደርገዋል ይላል፡፡ መዝ. 40-፡-1-3 ይህንን የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ በየዓመቱ ለ4 ጊዜ አብይ ድግስ በቀጨኔ ምዕራፈ ቅዱሳን የሰገነት ኪዳነምሕረት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ይደገሳል፡፡ እነዚህም፡-

  1. ሐምሌ 7 ቀን የአጋይስት ዓለም ቅድስት ሥላሴ ዓመታዊ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ፤
  2. በመስከረም ወር አዲስ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ዘመን መለወጫ ምክንያት በማድረግ፤
  3. የጌታ ልደት የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ፤
  4. የጌታን ትንሳኤ የፋሲካን በዓል ምክንያት በማድረግ ለነዳያን የምሳ ግብዣ ይደረጋል፡፡ ሉቃ. ም.14 ቁ.12

ጊዜያዊ ተረጂዎችን በተመለከተ

እለታዊ ችግር አጋጥሞአቸው በጣም ተቸግረው ወደ ማኅበሩ ጽ/ቤት መጥተው ለሚያመለክቱ ለጊዜያዊ ቀለብ የሚሆን ድጎማ፣ ለህክምና የሚሆን ገንዘብ፣ ወደቀያቸው ለሚመለሱ የመሳፈሪያ ትኬት በመስጠት አቅም በፈቀደ እየተረዱ በመሸኘትና በማጽናናት ያለንን ፍቅር እየገለጽን እንገኛለን፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡