ክብረ ቅዱሳን – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)
ስለክብረ ቅዱሳን ስናነሳ በቅድሚያ ማወቅ የሚገባን የእግዚአብሔርን ክብርና ቅድስና ነው፡፡

ምክንያቱም አንድ ሰው የፈጣሪውን ክብርና ቅድስና ማወቅ ካልቻለና ካልተረዳ የፈጣሪ የባሕርይ ክብር የባሕርይ ቅድስና ያልተረዳ ፍጡር የፍጡራንን የፀጋ ክብርና ቅድስና  መረዳት አይችልም፡፡ ወገኖች ሆይ ሠው መሆናችን የሚታወቀው ለፈጣሪ የምንሰጠው የአምልኮት ክብር የባሕርይው ነው ብለን ስናምን ነው፡፡ የዓለም ፈጣሪ የዓለም አስገኝ እግዚአብሔር ስለ ፍጥረቶች ምን ተናገረ ስንል ፈጥሮ መልካም እንደ ሆነ አየ የሚል ነው፡፡

 

                                   1.1 ክብርና ቅድስና
     የሰው ልጅ ክብር በሁለት አይነት መንገድ ይገለፃል፡፡

1ኛ  ትዕዛዝ ከመተላለፍ በፊት የነበረ ክብር፡- ይኽውም ማለት ኦሪት ዘፍጥረት /ዘልደት/ በተባለው ቅዱስ መጽሐፍ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ካለ በኋላ ከአንደኛው ቀን እስክ ስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት ልዩ ልዩ ፍጥረታትን ፈጥሮ ስድስተኛው ቀን ሲነጋ ከተፈጠሩት ፍጥረታት የተለየ ፍጡር መፍጠሩን እናያለን፡፡ የተለየ ያልንበት ምክንያት ለመጀመሪያዎቹ ፍጥረታት የፈጠራቸው አምላክ በቃሉ መልካም ሆነ መልካም ነው እያለ መጥቶ ሰውን ሲፈጥር ግን ሁለት ክበር ሲሰጥ እናያለን፡፡

  • የባህር ዓሣዎችን እንስሳትን አራዊትን በምድር ያለውን ሁሉ የሚገዛ የሁሉ አስተዳዳሪ ይሁን ብሎ ፈጠረ ይላል ዘፍ 1፡26፡፡
  • ሰውን በመልካችን በምሳሌያችን እንፍጠር ብሎ ክብሩን የሚወርስ በፀጋ የታጀበ ክብር የተጎናፀፈ አድርጎ በመፍጠሩ በስድስተኛው ቀን የፈጠረውን ፍጥረት አይቶ የተለየ መሆኑን ሲገልጽ  እጅግ መልካም አለ ዘፍ 1 ፡26-31 ሰውም እስከ ሰባት አመት በክብሩ እንደ ተፈጠረ ከብሮ ኖረ ያለ ኃጢአት ስለኖረና  ኃጢአትን  ስላልነካ ኃጢአትም ሰውን  አልነካችም ነበር፡፡

2ኛ ትዕዛዝ  ከመተላለፍ በኋላ ደግሞ የክብር ልብሱን ተገፈፈ ማለትም የማያልፍ ክብሩ ላይ የሚያልፍ ክብር /ውርደት/ተጨመረበት የሚያልፈውን  ውርደት የሚያጥብ እንደ ሣሙና  የሚያጠራ ፀፀት /ሀዘን/ የፍጡርና የፈጣሪ መለያ ምልክት ተሰጠው፡፡ ከመለያውም ጋርም መገናኛ  ንስሐ ተሰጠው፡፡ ለዚህም  ነው የሰው ክብር የሚታወቀው  የፈጣሪ ክብር ሲታወቅ ነው ያልነው፡፡ አባታችን አዳምም  ከበደል በኋላ ወደ ጫካ ገብቶ የእሱ ያልሆነውን የውርደት ልብስ ለበሰ ያውም በጊዜው ቅጠልን በመቀጠልም የሚያረጅ ልብስ ለበሰ የአምላክን ክብር ከእሱ ለይቶ አወቀ  ማወቁንም የምንረዳው ፈራሁ ማለቱን ሰምተን ነው፡፡ ዘፍ 3፡ 10  ከዚህ በኋላ የሰው ክብር እንደ መጀመሪያው  ክብር ሳይሆን  በትዕዛዝ የሚመላለስ ሆነ ይህ ማለትም የፈጣሪ ክብር የባሕርይ መሆኑን ፀንቶ መኖሩን  የፍጡር ክብር ደግሞ  የፀጋ ክብር መሆኑን የሚያሳይና እንደገናም ሰው በክብር መለያየቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ የክብር ልዩነት ስንል ግን በተፈጥሮ ልዩነት አይደለም፡፡ ጥቁር ፤ ቀይ፤ አጭር ፤ረጅም ፤ ሀብታም ፤ድሃ ፤ ካህን፤  ምዕመን፤ ባሪያ፤ ገዥ ፤ንጉሥ ፤ህዝብ፤ በሚል ክብር የተለየ ነው ማለት አይደለም  በመንግስቱ ጉዳይ እንጂ መንግስቱን ለማግኘት በትዕዛዝ ወደ እግዚአብሔር መመላለስ እና አድርግ አታድርግን በመጠበቅ በኩል ነው እንጂ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደ መሰከረ  የጠራችሁ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ እንዳለ 2ኛ ጴጥ 1፡ 15 በዚህ ቅዱስ  መጽሐፍ  ከቁጥር 14 ላይ ባለማወቅ አስቀድሞ የነበራችሁበትን ምኞት አትከተሉ የሚል ቃል እናገኛለን  የቀድሞው ምኞት ምን ነበር ብትሉኝ ዕፀ በለስን ለመብላት  የጓጓንበት ቀን ናት ክብር የሚል ቃል  አግኝተን  በምናስብበት ጊዜ የትኛው ክብር ላይ እንዳለን  ራሳችንን  በጥያቄ ውስጥ ማስገባት አለብን ሰው ከሞተ በኋላ ክብሩ የሚወሰነው በሐይማኖትና በስነ ምግባር  እንደሆነ እግዚአብሔር አምላካችን ለሙሴ እንዲህ ብሎ እንዲያስተምር ቅዱስ ቃሉን ነግሮታል፡፡እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዳለ ዘሌ 19፡ 2 የመግቢያ ያህል  ይህንን ካየን  በሚቀጥለው የቅዱሳንን ክብር  በዝርዝር እናያለን