የ34ኛ ዓመት የወንጌል አገልግሎት እነሆ – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

የ34ኛ ዓመት የወንጌል አገልግሎት እነሆ

በሃይማኖት ዕውቀት ማስፋፊያ ማህበር ጽ/ቤት መስከረም 6/2011ዓ/

የ34ዓመት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተጀመረበትን ዓመት

ምክንያት በማድረግ የቀረበ አጭር ታሪክ

እግዚአብሔር እረኛዬ ነው

ይህ መልእክት ለእስራኤል አንድ ጊዜ ተሰጥቶል የቆመ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ከሚነሳው ትውልድ ጋር ሲመላለስ የሚኖር የማያቋርጥ ትምህርት  ወንጌል ሲሆን በየጊዜው ተደጋግሞ ሊነገርም የሚገባው ነው፡፡

በእስራኤል መካከል በግ የሚያረባ ገበሬ ለበጎች ማደሪያ የሚሆን መግቢያውና መውጫው አንድ የሆነ ክብ ሆኖ በድንጋይ የታነጸ ጋጥ (በረት)ያበጁ ነበር፡፡ ፀሐይም መጥለቅ በሚጀመርበት ወቅት እረኛው ለምለም ሣር እያበላ ሲጠብቅ ከዋለበት መስክ የበጉን መንጋ ስብስቦ ወደ ማደሪያቸው ያስገባቸው ነበር፡፡

እረኛው ቀን እንደሚጠብቃቸው ሁሉ አውሬ እንዳይበላቸው ሌባ ሰርቆ እንዳይወስዳቸው ሌሊትም ቢሆን ራሱ ከመንጋው

ማደሪያ በር ላይ ተገኝቶ ይጠብቃቸው ነበር፡፡

በትንቢተ ሕዝቅ. ም.3 ቁ16 እንደተባለው የእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ ስለዚህ አንተ ሐጢአተኛውን ሰው ከክፉ መንገድ እንዲመለስ ነግረህ ባታስጠነቅቅውና ባሐጢአቱ ቢሞት ደሙን ከእጅህ እፈልጋለሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ከክፉ መንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው ወይም አስተምረኸው ሳይመለስ ቢሞት አንተ ነፍስህን አድነሃልና በሕይወት ትኖራለህ ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት እግዚአብሔር ባሕታዊ ገ/መስቀልን አስነስቶ ላከልን እኛም በቃሉ ተማረክን፡፡

እንዲህ ያሉትንም የመንፈስ ረሃብተኞች ከቸሩ እረኛቸው ከክርስቶስ ጋር ልናስተዋውቃቸውና ከማዕድም ተመግበው  እንዲጠግቡ ልናደርጋቸው ታዘናል፡፡ የአውሬውም እራት እንዳይሆኑ ልንጠብቃቸው ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌም እረኛ በጎቹን የለመለመ ሣር እንዲነጩ የጠራ ውኃ እንዲጎነጩ ወደ መስክ የሚያሰማራቸው ከተኩላና ቀበሮ አፍ የሚጠብቃቸው ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለበጎቹ ጥቅምና ደኅንነት ጭምር የሚያስብ መሆን አለበት፡፡

የመንጋው ጠባቂ የሆነው እውነተኛው እረኛችን ክርስቶስ ግን ስለበጎቹ ሕይወቱን ከመሰዋቱም  ሌላ የመንፈስ እረኃብተኞች ለሆነው ሁሉ ሕይወት መድኀኒት የሆነውን ቅዱስ ሥጋውን ዘወትር ይመግበናል፡፡ በመንፈስ ጥም ተይዘን ለምንሰቃየውም ክቡር ደሙን ጠጥተን እንድንረካ ሰጥቶናል ወደ እርሱም የምንመጣውን ወደ ውጭ አያወጣንም፡፡ሰለዚህ ነው ዳዊት እግዚአብሔር እረኛዬ ነውበለመለመ መስክ ያሳድረኛል ወደ እረፍትም ውኃ ይመራኛል ያለው፡፡

በዚሁ እንጻር የእረኝነት ምሳሌ የተሰጠን አገልጋዮች ሁሉ የምንጠብቃቸው የእግዚአብሔር ልጆች ኑሮአቸውን የሚቀናበትን ክርስቲያናዊ ሕይወታቸው የሚደገፍበትን ሃይማኖታቸው የሚጠበቅበትን መንገድ እናዘጋጅላቸው የእረኝነት ትርጉም ይህ ነውና፡፡

በዚሁ በኢትዮጵያ ሀገራችን ምድር በሸዋ ቡልጋ ከአቶ ኃ/መስቀል ገ/ወልድ ከወ/ሮ አባይነሽ በየነ የተወለዱት ሊ/ትጉ/መ/ር ገ/መስቀል ኃ/መስቀል በመስከረም ወር በ1978 ዓ/ም በአትኩዋር ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ በምህላ ፀሎትና በስብከት ይህንን መንፈሳዊ ጉባዔ መሰረቱ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

በመቀጠልም በተወለዱበት አካባቢ እየተዘዋወሩ በማስተማርና የጣኦት ዛፎችን በመቁረጥ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ ጥረት ሲያደርጉ ከቆዩ በኃላ መንግስት ደን ያለማል ገ/መስቀል ደን ይጨፈጭፋል የደርግ መንግስት ይጠፋል ብሏል በማለት ግንቦት 24 ቀን 1978 ዓ/ም በወታደሮች ተይዘው ወደ ደብረብርሃን እስር ቤት ተጋዙ ከዚያም ፍርድ ቤቱ ሲያሰናብታቸው ወደ ሳሪያ ሚካኤል ኩክየለሽ ዋሻ በመግባት በሽተኞች በማስጠመቅ የጨሌ ጣኦት በማስጣል በሰንበት ወንጌል በመስበክ ሲያገለግሉ ከቆዩ በኃላ ወደ ደብረብርሃን ደብረ ጽባሕ ቅ/ጊዮርጊስ ቤ/ክ ሄደው እንዲያስተምሩ ትዕዛዝ ደርሶአቸው በ1981 ዓ/ም ከብፅዑ አቡነ ኤፍሬም ቡራኬና ፍቃድ ተቀብለው መቃብር ቤት በመቀመጥ በሽተኞች ተጠምቀው እንዲፈወሱ ንስሐ እንዲገቡ ድሆች እንዲረዱ በማድረግ ሰፊ ሥራ እየሰሩ ሳለ ወደ ወይንዬ ተ/ሃይማኖት ቤ/ክ እንዲሄዱ ታዘዙ በዚያም ሄደው ገዳሙን አስገድመው በስብከትና በፀሎት ከቆዩ በኃላ ወደ አዲስ አበባ ደ/ሰ/ቀጨኔ መድሐኒአለም ቤ/ክ መጥተው እንዲያስተምሩ ታዘዙ በ1983 ዓ/ም መስከረም 28 ቀን ወደ አዲስ አበባ መጥተው የታዘዙትን ሥራ ሲጀምሩ ጥቂት ሰዎች በመሰብሰብ ነበር፡፡ ከዚያም በምህላ ፀሎት በቄደር ጥምቀት በሰርክ ጉባዔ የበጎ አድራጎት ሥራ በመስራት ሰው እየበዛ ሥራው እየሰፋ ሄደ ከዚያም በቀጨኔ ደ/ሰ/ መድሐኒዓለም ቤ/ክ ብቻ መሆኑ ቀረና በሁሉም አድባራትና ገዳማት ተስፋፋ በየቤተክርስትያናቱ ግቢዎች እስኪጠቡ ድረስ እጅግ ሰፊ ጉባዔ ሆነ ሰይጣን በዚህ ጉባዔ በመቅናት መ/ር ገ/መስቀል  አንዲታሰሩ አደረገ በፍርድቤት ፈቃድ ሳይኖርህ ይህንን ያክል ህዝብ መሰብሰብ አትችልም አሁን የምንለቅህ ፍትህ ሚኒስቴር ሄደህ ፍቃድ የምታመጣ ከሆነ ብቻ ነው አሏቸው እሺ አወጣለሁ ብለው በዋስ በመለቀቅ በ1987 ዓ/ም በሰኔ ወር ፍትህ ሚኒስቴር ህጋዊ ፈቃድ ሰጣቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በህጋዊ ፈቃድ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ከዚያም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ዓለምን ዞረው ወንጌል እንዲሰብኩ እግዚአብሔር ስለፈቀደላቸው የወንጌሉን ቃል በመስበክ ንስሀ እንዲገቡና የበጎ አድራጎት ሥራ እንዲሰሩ አድርገው ተመልሰዋል፡፡ በርካቶችንም በማስጠመቅ ክርስቲያን እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡

ቅዱስ ወንጌል እንደሚለው በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ እንደሚል ሊ/ት/መ/ር/ገ/መስቀል በቤተክህነትና በመንግስት ተፅዕኖ በደርግ 9 ጊዜ በኢሀዲግ 6 ጊዜ በጠቅላላው 15 ጊዜ ወደ እስር ቤት ተጉዘው በፍርድ ቤት በነፃ ተለቅቀው ያለድካም ለሊትና ቀን በመስራት ይህንን አሁን የተሰበሰብንበትን ቤተ ፀሎትና የስብከተ ወንጌል አዳራሽ በማሰራት የኪዳነ ምህረት ፅላት አስገብተው ሰፊ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ፡፡

ውድ ወገኖች በዚህ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ጠንካራና የጸኑ ምዕመናን ስላሉ ከ800 በላይ የገጠር ቤ/ክ እንዲታደሱና አዳዲስ እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡

ችግረኛ ወገኖቻችን በየዘርፉ እንዲረዱ በማድረግ ሰዎችን ለንስሐ በማብቃት የቄደር ጥምቀትና ለበሽተኞች የቀንዲል ጥምቀት እንዲአገኙ በማድረግ መምህራን በመንፈሳዊ ኮሌጅ ተምረው እንዲያስተምሩ በማድረግ ሰፊ ሥራ ሰርተው እያሰሩን ይገኛሉ  እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

የዛሬውም በዓል ለማክበር የቻልነው ብዙ ውጣውረድ አሳልፈን ነው፡፡ ታሪኩን በሰፊው ከሕይወት ታሪክ መፅሀፋቸው ላይ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡ በዚህ ማህበር ውስጥ ፍቅር አንድነት ፅናት እያደገ በመሄዱ ጠላት ሊከፋፍለን አልቻለም አሁንም በዚሁ መንገድ በመጓዝ ከዚህ የበለጠ መልካም ሥራ ሰርተን ለመገኘት እንድችል ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ይርዳን በዓሉን የበረከት የሰላም በዓል ያድርግልን አሜን ፡፡

                                                                                                                     ከማኅበሩ ጽ/ቤት

Share this

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *