ጥያቄና መልስ – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

በግዐ ፋሲካ

የሃይማኖት ዕውቀት ማስፋፊያማህበር ሐዋርያዊ ተልዕኮውን  ለሰላሳ ሶስት /33/ ዓመት ወንጌልን በሁሉ ቦታ ይደርስ ዘንድ በሊቀ ትጉኃን መ/ር ገ/መስቀል ኃ/መስቀል መሪነትና መስራችነት አገልግሎቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ከአገልግሎቱም ውስጥ ለየት ያለውንና በሌላው መድረክ (አጥቢያ) ያልተለመደው ማህበራችን በወር ሁለት ጊዜ የጥያቄና መልስ መርሀ ግብር በማዘጋጀት ምዕመናን የተለያዩ መጻሕፍቶችንና መጽሔቶችን አንብበው ያልገባቸውን እንዲሁም መምህራን በየመድረኩ ሲያስተምሯቸው ግልጽ ያልሆነላቸውን ጥያቄ በአካልና በጽሁፍ ይዘው እንዲቀርቡ በማመቻቸት ይህንን መርሃ ግብር አዘጋጅተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ ለዛሬ ከተጠየቁት ጥያቄዎች መካከል በጊዜው መልስ ተሰጥቶባቸው በዚህ ክፍል እንዲወጣ የተዘጋጀውን አብረን እናያለን፡፡

ጥያቄ፡– በብሉይ ኪዳን እስራኤላዊያን የፋሲካውን በአል በግ አርደው ያከብራሉ ይላል፡፡ በዘጸ 12፡ 1-14 ድረስ ያሉ ቃላቶችስ ትርጉማቸው ምንድነው?

መልስ፡- እስራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ ከታዘዘው መቅሰፍት እንዲድኑ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በማዘዝ እያንዳንዱ እስራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርዱ ደሙን በበሩ /በመቃኑ) እንዲቀቡ ታዝዘዋል ትዕዛዙንም ፈጽመዋል፡፡ የታዘዘው መልአክም የደም ምልክት የሌለበትን የግብፃዊያንን ቤት እየመታ የደም ምልክት ያለበትን የእስራኤላዊያንን ቤት እያየ ያልፍ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እስራኤላውያን በየአመቱ ሚያዝያ በባተ በ14ኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በአል ያከብሩ ነበር፡፡ በጉ ንጹህ ቀንዱ ያልከረከረ የእግሩ ጥፍር ያልዘረዘረ ጠጉሩ ያላረረ ዓመት የሆነው ነበር፡፡  ይኸውም የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ቀንዱ ያልከረከረ፣ ጠጉሩ ያላረረ፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረ የሚለው ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ ሰው ቢሆንም በልቡ ትዕቢት፣ በእጁ በደል እንዳል ተገኘበት ለማሳየት ነው፡፡ በነገሩም ሆነ በተግባሩ ኃጢአት አልተገኘበትም፡፡ ግፍን አላደረገም፣ በአፉም ሐሰት አልተገኘበትም ነበር፡፡ እንዲል ት/ኢሳ 53፡9 እንዲሁም ባለቤቱ ለፈሪሳዊያን ስለ ኃጢአት የሚወቅሰኝ ማን ነው ብሎ ገስፆዋቸዋል ንፁሐ ባህርይ ነውና ዮሐ 8-፡-46 እስራኤላዊያን ሙሴ እንዳዘዛቸው በጉን አርደው ደሙን መቃናቸውን ቀብተው ከመቅሰፍት ድነዋል፡፡ ሞተ በኩር በታዘዘ ጊዜም የተቀባውን መቃን እያየ ያልፍ  (ይተው) ነበር፡፡ ፍፃሜው ግን በበግ የተመሰለው የኢየሱስ ክርስቶሰ ሥጋውና ደሙን በሚቀበሉ ምእመናን ላይ አጋንንት አይበረቱባቸውም ለማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን ነውርና እድፍ እንደ ሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ ብሎ ጽፏል፡፡ 1ጴጥ 1-፡-18-22 ከዚህ ቀጥሎ ያሉት በዚህ ምዕራፍ የተነገሩ ከሐዲስ ኪዳን ሊቃውንት አስተምህሮ ጋር ሲተረጎም

  • ጥሬውን አትብሉ፡- መባላቸው ሥጋውና ደሙ ስትቀበሉ መለኮት የተለየው ነፍስ የተወሃደው ነው አትበሉ ማለት ነው፡፡
  • በእሳት ጠብሳችሁ ብሉት፡- መባላቸው በእሳት የተጠበሰ ሙቀት እንደማይለየው ሁሉ ደሙም መለኮት የተወሃደው ነፍስ የተለየው ነው ብላችሁ አምናችሁ ቅረቡ ሲል ነው፡፡
  • በውሃ የተቀቀለውን አትብሉ መባላቸው፡- በኢየሱስ ክርስቶስ መነሳት አትጠራጠሩ እንደ ፍጡራን መበስበስ መፍረስ አለበት አትበሉ በኩረ ትንሳኤ ሁኖ ከሙታን መካከል በኃይሉ በስልጣኑ ተነስቷል ብላችሁ እመኑ እንጂ ማለት ነው፡፡
  • ከመራራ ቅጠል ጋር ብሉት፡- ክቡር ደሙ ቅዱስ ሥጋው ለመቀበል ተዘጋጅታችሁ ተቀበሉት ለአፋችሁ ምሬት እስኪ ሰማችሁ የበላችሁት ከሆዳችሁ እሰኪጠፋላችሁ አስራ ስምንት ሰዓት ፆማችሁ ተቀበሉት ማለት ነው፡፡
  • ኩፌት ደፍታችሁ፡- በራሱ ላይ የተደፋውን አክሊለ ሦክን እያሰባችሁ ኑሩ ሲለን ነው፡፡
  • በትር ይዘችሁ፡- መከራ መስቀሉን እያሰባችሁ፡፡
  • ዝናር ታጥቃችሁ፡- ከዲያብሎሳዊ አሰራር ነፃ ሁናችሁ በንፅህና ኑሩ፡፡
  • ጫማ ተጫምታችሁ፡- ሃይማኖት ከምግባር አይለይምና ምስጢረ ወንጌልን ተምራችሁ ምግባር ሰርታችሁ ኑሩ ሲለን ነው፡፡
  • አጥንቱን አትስበሩ መባሉ፡- የጌታችን አጥንት እንደማይሰበር ለማመለክት ነው ዮሐ 19-፡-33 በንግግራችሁ አጥንትን የሚሰብር ውስጥን የሚነካ ንግግር ከአፋችሁ አይውጣ ከባህርይ አባቱ እንደለየው እንደ አርዮስ ወልድ ፍጡር ብሎ እንደ ካደ አትካዱ፤ እንደ ፈሪሳዊያን ዕሩቅ ብእሲ ተራ ሰው ነው አትበሉ እንደ ዘመናችን ሃሰተኞች መናፍቃን ደግሞ አማላጅ ነው አትበሉ ማለት ነው፡፡
  • እየቸኮላችሁ ብሉት፡- ማለቱ በንስሐ ከሀጢአት ነጽታችሁ ዕለተ ሞታችሁም እያሰባችሁ ነቅታችሁ ተግታችሁ ኑሩ መልካም ሥራ ለመስራት አትታክቱ ለነገ አትበሉ ማለት ነው፡፡
  • በልታችሁ የቀረውን በእሳት አቃጥሉት፡- የመረመራችሁትን መርምራችሁ የቀረውን ከአዕምሯችሁ በላይ የሆነውን ለእግዚአብሔር ስጡት መንፈስ ቅዱስ ያውቃል በሉ ሲል ነው፡፡ ይቀጥላል. . . .