ጾመ ኢየሱስ – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

ጾመ ኢየሱስ

ክብር ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾው ጾም ‹‹ጾመ ኢየሱስ›› ይባላል፡፡
• ጾም ‹‹ጾመ ጦመ›› ከሚል የግእዝ ግሥ የወጣ ሲሆን፣ ጾመ ማለት እህል ውሃ ሳይቀምስ ዋለ፣ ሥጋ ከቅቤ ተከለከለ ማለት ነው፡፡(ትን. ዳን 10÷3)
• ጸም ጦም ማለት ሲሆን ጊዜ ሳይደርስ እንዳይበላ፣ እዳይጠጣ የሚከለክል ሕግ በቅዱስ መጽሐፍ የታዘዘ የጸሎት ወንድም ማለት ነው፡፡ (ተን. ኢዩ 1÷14፣ 2÷15)
• ጾም ቤሌላ አነጋገር ልጓም ይባላል፡፡ ይህም ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓ መጽሐፉ ‹‹ጾም ልጓም ፍሬሐ ጥዑም ትሕተ ኢናምስላ ለጾም ትርጉም ጾም ልጓም ናት ፍሬዋም ጣፋጭ ነው ጾምን የተናቀች አናድርጋት (ጾመ ድጓ) ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡ ልጓም የሰም አነጋገር ሲሆን ጾም ወርቅ ነው፡፡ ጾም ልጓም ናት ማለቱ በልጓም ፈረሶች ይገታሉ በጾምም የሰው ልጅ ሰውነቱን ከኀጢያት ሥራ ይገታበታልና፡፡ ፍሬዋም ጣፋጭ ነው ማለቱ ጹመን የምናገኘውን ክብር መግለጡ ነው፡፡ ስለ ጾም ባጭሩ ይህንን ካልን ስለ ጾመ ኢየሱስ እንቀጥላለን፡፡
                                                    ጾመ ኢየሱስ የተለያዩ ስሞች አሉት
1. ጾመ ኢየሱስ ይባላል

ጾመ ኢየሱስ የተባለበት ምክንያት ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኃላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሄዶ በዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከዘረጋ ሳያጥፍ ከቆመ ሳይቀመጥ እሱ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ከርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው፡፡
2. ጾመ ሁዳዴ ወይም ሁዳዴ ጾም ይባላል
እንዲህ የተባለበት ምክንያት በቀድሞ ዘመን የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁሉም ሁዳድ፣ ሁዳዴ ይባል ነበር፡፡ ታዲያ ይህን የመንግሥት እርሻ ሕዝቡ ሁሉ ወንድ ሴት፣ ሽማግሌ ወጣት ሳይባል ለማረስ ወይም ለመሥራት ይወጣ ነበር፡፡ ጾመ ኢየሱስም የንጉሠ ሰማይ ወምድር የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ስለሆነ ሁዳዴ ተብሏል፡፡ የንጉሡን እርሻ ወንድ ሴት፣ ሽማግሌ ወጣት ሳይባል ወጥተው እንዲሰሩት የጌታችን የኢየሱስ ከርስቶስንም ጾም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያ ኖች ሁሉ ወንድ ሴት፣ ሽማግሌ ወጣት ሳይባል ባንድነት የሚጾሙት የአዋጅ ጾም ስለሆነ ሁዳዴ ተብሏል (ትን. ኢዩ 2÷15)፡፡


3. በዓተ ጾም ይባላል
ይህም ማለት የጾም መግቢያ፣ መባቻ፣ መጀመሪያ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት ማለት ነው ለሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መሰረታቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ነውና፡፡
4. ጾመ አርብዓ ይባላል
ጌታችን የጾመው አርባ ቀን በመሆኑ ነው (ማቴ. 4÷1)
5. ዓቢይ ጾም ይባላል
ይህም ‹‹ዓቢይ እግዚአብሔር ወብዙኅ አኮቴቱ ትርጉም እግዚአብሔር ታላቅ ነው ምስጋናውም ብዙ ነው ማለት በሰማይና በምድር በአየርና በእመቅ የመላ ነው›› (መዝ 7÷1) ተብሎ የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ዓቢይ ጾም ተብሏል፡፡
6. ጾመ ሙሴ ይባላል
ይህም ቅዱሳ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ‹‹ከመዝ ይቤ ሙሴ፣ እስመ ለዓለሙም‹‹ ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት›› እያለ በጾመ ድጓ ስለዘመረ ወይም ስላመሰገነ ጾመ ሙሴ ተብሎም ይጠራል፡፡
7. ርዕሰ አጽዋማት ይባላል
• ርዕሰ አጽዋማት የተባለበት ምክንያት ‹‹ውእቱ ርዕስ ወንህነ አባል ትርጉም እሱ ራስ እኛ አካል ነን›› ተብሎ የተነገረለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመውና የአጽዋማት ሁሉ ራስ ስለሆነ ነው እንዲሁም በቁጥር ብዛት ከሌሎች አጽዋማት የጾመ ኢየሱስ የቀናት ብዛት ብዙ ወይም ሃምሳ አምስት ቀናት ስለሆነ ነው፡፡
• ታዲያ ጾሙን ስንጾም ከእህል፣ ከውሃ ብቻ መከልከል ሳይሆን ከነገርም፣ ከተለያዩ ኀጢያቶችም እራሳችንን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል፡፡ ‹‹ይጹም ዓይን ይጹም ልሳን ዕዝንኒ ይጹም እንሰሚዓሕሱም በተፋቅሮ ትርጉም ዓይን ይጹም አንደበት ይ ጹም ጆሮም ክፉ ሰምቶ ያን ከመናገር ይጹም (ይከልከል) በፍቅር›› (ጾመ ድጓ) እንዲል፡፡
ስለሆነም ጾሙን በትህትና፣ በጸሎትና በስግደት ጭምር ፍቅርን እንደ ሸማ ተላብሰን ለመጾምና የበረከት ሰዎች እንድሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የመጀመሪያውን ሳምንት ዘወረደ እየተባለ የሚጠራውን እናያለን፡፡
                                                                          ዘወረደ
የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ከእሁድ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ ዘወረደ ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለትም የወረደ ወይም የወረደው ማለት ሲሆን አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ መወለዱንና በመስቀል መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው (ዘፀ 3÷9፣ ዮሐ 3÷13) ቅዱስ ያሬድም ሰውን ለማዳን የወረደውን ከእመቤታችን የተወለደውን አይሁድ እንደሰቀሉት እንዲህ ይገልጻል፡፡
‹‹ዘወረደ ዕምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ ትርጉም ከላይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት በቃሉ ተናግሮ የሚያድን የሁሉ ጌታ መሆኑን ባያውቁ›› እንዲል (ጾመ ድጓ ዘዘወረደ)
2ኛም ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ ይህም እንዲህ ነው ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) የሚባል የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር፡፡ በ714 ዓ/ም እንደነበረ ይነገራል፡፡ ይህ ጾም በስሙ የተሰየመበት ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወረው የጌታችንን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ምዕመናን መስቀሉን ወደ ፋርስ ወርዶ እንዲያስመልስላቸው ለመኑት እሱም ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ ዕድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ምዕመናንም ይህን ሐሳቡን ደግፈው መስቀሉን አምጣልን እንጂ የአንድ ሰው ዕድሜ ቢበዛ ሰባና ሰማንያ ነው ጾሙን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን አሉት በዚህ ተሰማምቶ ወደ ፋርስ ዘምቶ መስቀሉን አስመልሶላቸዋል፡፡ እነሱም 5 5 ቀን ተከፋፍለው ጹመውለታል፡፡ ከዚያ በኃላ የተነሱ አባቶችና ምዕመናንም ሁሉ ጹመውታል፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ጾሙን ጹመው ምዕመናንም እንዲጾሙት ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ጾሙም ከዓቢይ ጾም ጋር በመጀመሪያ እንዲጾም አድርገዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ጋር በመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ እንዲጾም አድርጋለች እኛም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች ይህን ጾም እንደ አባቶቻችን ጾመን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ለማግኘት ያብቃን አሜን፡፡

በመጋቢ ሀዲስ መምህር ዳንኤል አለባቸው

Share this

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *