ነገረ መለኮት – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

ናሁ ንጽሕፍ ነገረ እበያቲሁ ለእግዚአብሔር

ትርጉም  የእግዚአብሔር የገናንነቱን ነገር ከብዙ  በጥቂቱ  ከረጅሙ በአጭሩ እነሆ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ እንጽፋለን፡፡ ነገረ መለኮት የሚለው ቃል ብዙ ነገርን የሚተነትን ሆኖ በአጠቃላይ፤ መለኮት የሚነገርበት ትምህርት፤ በሥነ- መለኮት የሚደረግ ጥናት፤ ህልዎቱን፤ ስሙን፤ ባህርዩን ወዘተ . . . የሚያመላክት ነው፡፡ የነገረ መለኮት ትምህርት ስለ እግዚአብሔርና እግዚአብሔር ከዓለም (ከፍጥረት) ሁሉ ጋር ስላለው ግንኙነት የሚያጠና ዘርፍ ነው፡፡ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ትውልዱን ለመታደግ የነገረ መለኮት ጥልቅ ጥናት ትልቅ ሚና አለው፡፡ መለኮትን ያህል በሰው አእምሮ ማጥናት ማለት ፍጡር ፈጣሪውን ማጥናት ቢሆንም ስለ መለኮት ፍጹም ዕውቀት ይኖረናል ማለት የማይታሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ከአየነው ከሰማነው ከአነበብነው ከእግዚአብሔር ቃል ዋና ዋናውን መርጠን ስለእግዚአብሔር ማንነት መግለጽ ስለፈለግን ነው፡፡ ስለዚህ  መለኮት ወይም ፈጣሪ እርሱ ራሱ በፍጥረቱ አማካኝነት ለፍጥረቱ በገለጠውና በተገለጠው ለእኛ በሚመጥነን መልኩ በቅዱሳኑ በኩል በሰጠን ቃሉና መልዕክቱ እንዲሁም በሚወደው ልጁና በእቅፉ ያለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ አባቱ በተረከልንና ባስተማረን መሠረት አቅማችን በፈቀደ መልኩ በጸጋው ተደግፈን ስለነገረ መለኮቱ ሀልዎቱ አምላክነቱ ፈጣሪነቱ ስሙ አማን አማን እብለከ ከመ ዘነአምር ንነግር ወበዘርኢነ ሰማዕተ ንከውን ወስማዕነሰ ተአብዩነ ነሢአ እውነት እውነት እልሃለሁ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን ምስክርነታችንንም አትቀበሉትም፡፡ እንዳለ በዮሐ. ምዕ 3፡11 የጽሁፉ ዋና አላማ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ማንነት አንድነትና ሶስትነት ማሳወቅና ማስረዳት ነው፡፡ ወደ ዋናው ጽሁፍ ከመግባታችን በፊት ለማስገንዘብና ለማሳወቅ የፈለግነው ነገር ከአሁን በፊት ከአነበብናቸው መጽሔቶችና ልዩ ልዩ መጻሕፍቶች ውስጥ ያላገኘነውና ያልታተመ ያልተብራራ የተለየ አተረጓጎምና ትንታኔ ይዘት ያለው ጽሁፍ ይዘንላችሁ ስለቀረብን ውድ አንባቢያን ጽሁፉን በምታነቡበት ሰዓት በሰከነ ህሊና ሆናችሁ ያለምንም መደናገር እንድታነቡትና እንድትረዱት ስንል በልዑል እግዚአብሔር ስም አደራ እንላለን፡፡

ንግባዕኬ ኃበ ጥንተ ነገር ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ ቅዳሴ ማርያም ቁጥር 79 እግዚአብሔር ማነው? ሥራውስ ምንድነው? ይህንን ዓለም እንዴት ፈጠረው? አለምን ከመፍጠሩ በፊት እንዴት ባለ ሁኔታ ይኖር ነበር? የሚል ጥያቄ በአእምሯችን ለሚመላለስብን ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ማንነትና ሥራ ለመግለጽና ለማብራራት ቅዱሳት መጻህፍትን ዋቢ በማድረግ የተቻለንን ያህል እንሞክራለን ከስሙ ትርጓሜ ስንነሳ እግዚ ማለት ገዥ ጌታ ሲሆን  ገዝዐ ገዛ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ ሲናበብ እግዚአብሔር የሚል ዐረፍተ ነገር ይሰጣል የስሙ ትርጓሜ የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም የማይዳሰሰውን ረቂቁን የሚዳሰሰውን ግዙፉን ፍጥረት ፈጥሮ የሚገዛ የባሕርይ አምላክ ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እግዚአብሔር በሚለው ስም መጠራት የጀመረው ይህንን ዓለም ከፈጠረበት ዕለት ጀምሮ ነው፡፡ ስንል እግዚአብሔር በፊት የለም ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ አለምን ከመፍጠሩ አስቀድሞ በአንድነት፣ በሶስትነት፣ በመንግስት፣ በስልጣን፣ በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ በከሐሊነት ጸንቶ እንዴት ሲመሰገን ሲቀደስና ሲወደስ እንደነበረ ከማይመረመረው ቀዳማዊ ረቂቅ ባሕርዩ ለመግለጽ ስለፈለግንነው እንጂ እግዚአብሔር አለምን ከመፍጠሩ በፊት በባሕርዩ ንጉሥ ነው፡፡ የተወደዳችሁ ወድ ክርስቲያኖች በሙሉ በተረጋጋ መንፈስ በዚህ ጽሁፍ የመለኮትን ምንነት እንወቅ እንላለን፡፡ ይቀጥላል . . .