ልሳነ ምዕመናን – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

ልሳነ ምዕመናን

ጥያቄ፡- በቅድሚያ እራስዎን ያስተዋውቁን

መልስ፡- እኔ አቶ ነጋሽ አያኔ እባላለሁ ወይም ወልደ ሐዋርያት ወደ ክርስትናው አለም በደንብ የተቀላቀልኩትና የተጠራሁት ለንስሃ ጥምቀት ወደ ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን በሄድኩበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ልክ እንደ ጴጥሮስና እንደ ወንድሙ እንድርያስ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት በባህር አካባቢ አሳ ለማጥመድ ጎንበስ ቀና ደፋ እያሉ ሳለ የኛ ጌታ ሳያስቡት ድንገት በማቴ ምዕ 4-፡- 19- 20 በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው፡፡ ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት፡፡ ማለት በአለም ላይ የነበራቸውን አስተሳሰብ ትተው አዲሱን የክርስቶስን አስተሳሰብ በፍቅርና በሰላም በምህረት ሰዎችን እንዲጠሩ አደረጋቸው፡፡ እኔም አቶ ነጋሽ አያኔ ወይም ወልደ ሐዋርያት ባጋጠሚ ለንስሃ ጥምቀት በሄድኩበት ሰኔ 1983 ዓ.ም በንስሀ ጥምቀት ከአባታችን ሊቀ ትጉ/ ባሕታዊ መ/ር ገ/መስቀል ኃ/መስቀል ጋር በዚች አጋጣሚ ልክ እንደ ሐዋርያት ጥሪ ደረሰኝ ይህንን ድምጽ የሰማሁትና ከአባታችን ጋር የተገናኘነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን በታደገበትና ባዳነበት በዕለተ አርብ ቀን ነበር፡፡ ይህች ቀን ለእኔ የመጨረሻዬ የመዳን ጥሪን የሰማሁባት ቀን ነበረች፡፡ የእኔን ጥሪ ለየት የሚያደርገው የአለምን ኃጢያት ባስወገደበት ቀን በመጠራቴ ሁልጊዜም ደስ ይለኛል፡፡ እግዚአብሐር ይመስገን፡፡ ይህ ጥሪ እንደደረሰኝ ምን ማድረግ አለብኝ የሚል ሀሳብ ወስጤን አቀጣጠለው ከዚያም ወደ ዉስጤ አንድ ሐሳብ መጣልኝ አንድ አሮጌ ታክሲ ነበረችኝና ሐዋርያትን ሰው አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ የአለው ቃል ወደ ዉስጤ ገባና እኔስ ታዲያ ምንድነው የማጠምደው ስል በአሮጌዋ ታክሲ የእግዚአብሔርን ባሪያ አባታችንን ባመላልስ ነው የኔ የስራ ድርሻ ብየ ወሰንኩኘ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለነበር ያለምንም ችግር ከአባታችን ጋር በመሆን በታክሲዋ እየዞርን ወንጌልን እንሰብክ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባም አልፎ እስከ ሸኖ ድረስ በማጓጓዝ አገለግል ነበር፡፡

 

ጥያቄ፡- በዚህ አገልግሎት ወስጥ ያጋጠማችሁ ችግር ነበር

መልስ፡- 1984 ቅዳሜ ቀን በጧት ልደታ ቤተክርስቲያን የአውደ ምህረት መከልከል ገጥሞናል የተከለከልንበት ምክንያት ልክ እንደ ክርስቶስ ዘመን የእግዚአብሔር መንፈስ በጣም ይሰራ ነበር:: በሽተኞች ይፈወሱ ነበር:: አጋንንት ይወጡ ነበርና የተከለከልነው በቅናት ዲያብሎስ ስለቀና ጥላቻውን በወንድሞቻችን ላይ አሳድሮ በስጋ ተገለጠ:: አውደ ምህረቱን ዘጋብን መፍትሔ መስሎት፤ የእኛ እራይ ግን ብዙ እስራቶችም ሆነ ብዙ ዲያብሎሶችም ቢነሱ ሊያቆመው የሚችል አልተገኘም ተልዕኮው ከእግዚአብሔር ስለነበር ነው፡፡ ይህ የወንጌል ተቃውሞ ለሐዋርያትም ገጥሟቸው ነበር፡፡ በሐዋ. ም. 5-፡-33-42 ይነበብ እነርሱም ሲሰሙ በጣም ተቆጡ ሊገድሉአቸውም አሰቡ፡፡ ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የከበረ የህግ መምህር ገማልያ የሚሉት ከጉባኤው ተነስቶ ሐዋርያት ከእነሱ ፈቀቅ እንዲያደርጉ ካዘዘ በኋላ የእስራኤል ሰዎች ሆይ ስለነዚህ ሰዎች ምን እንደምታደርጉ ለራሳችሁ ተጠነቀቁ፡፡ ከዚህ ወራት አስቀድሞ አንድ ቴዎዳስ የሚባል ሰው እኔ ታላቅ ነኝ ብሎ ተነስቶ ነበርና አራት መቶ የሚያህሉ ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባበሩ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበተኑ እንደ ምናምን ሆኑ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰዎች በተጻፉበት ዘመን የገሊላዉ ይሁዳ ተነስቶ ነበር ብዙ ሰዎችንም አሸፍቶ አስከተለ እርሱም ጠፋ የሰሙትም ሁሉ ተበታተኑ፡፡ አሁንም እላችኋለሁ ከእነዚህ ሰዎቸ ተለዩ ተዋቸውም ይህ ሃሳብ  ወይም ይህ ስራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና፤ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ ግን ታጠፏአቸው ዘንድ አይቻላችሁም፤ በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ፡፡ የአባታችንም ተልእኮ ከእግዚአብሔር ስለነበረ እስራትም ሆነ ተቃውሞም ሊያቆመው አልቻለም ከቀን ወደ ቀን የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ይሄድ ነበር፡፡

  • 2ኛው ተቃዉሞ በ1985 የአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በር ተዘግቶብን ለሰባት ቀን መንገድ ላይ የተደረገ ጸሎት አሁን የባቡር ትኬት መሸጫ የሆነው ቦታ ላይ ነበር፡፡ ለሰባት ቀን የጸሎት ጊዜ አሳለፍን እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ በዚህ ውጣ ውረድ ሁሉ እንድናለፍ የእሱ ፈቃድ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ተቃውሞ ቢገጥመንም እንኳን ከጸሎቱ መርሃ ግብር ግን ማንም ሊያቋርጠን አልቻለም፡፡ የእግዚአብሔር አላማና ዕቅድ ሰለነበር ነው፡፡ የሰው ሃሳብ ቢሆን ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ መራመድ አይቻልም፡፡ ይቀጥላል. . .