ግንቡ ፈረሰ – የሃይማኖት ዕዉቀት ማስፋፊያ ማህበር (የሃ.ዕ.ማ.ማ)

ግንቡ ፈረሰ

ጥር ፯ ቀን የሥላሴ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በደመቀ መልኩ በማኅሌት ፣ በቅዳሴ ፣ በመዝሙር ፣ በምስጋና እና ወንጌልን ለምዕመናን በማስተማር ይከበራል። አሁን የሥላሴ በዓል ይከበራል ስንል ሥላሴ በአንድ ቀን ብቻ ታስበው ይቀራሉ ማለት አይደለም ምንም ሁልጊዜ ተአምር ሠሪ ቢሆኑም በትዕቢተኞች ላይ ልዩ ተአምር የሠሩበትን ቀን ለሰው ለማሳወቅ ነው እንጂ።
ጥንተ ነገሩ እንዲህ ነው ከጥፋት ውኃ በኋላ የኖኅ ልጅ ካም ኩሽን ወለደው ፣ ኩሽም ናምሩድን ወለደው። ናምሩድም በምድር ላይ ኃያል እና አዳኝ ነበረ። ናምሩድን ጨምሮ ሌሎችም የኖኅ የልጅ ልጆች ሁሉ በአንድነት ይኖሩ ነበር። ከምሥራቅ ተነሥተው ወደምዕራብ ሀገር ሲሄዱ በሰናዖር ምድር ሰፊ ሜዳ አገኙና በዚያ መኖር ጀመሩ። ከዚያ በኋላ፦
“እርስ በርሳቸውም ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ። ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው፤ የምድርም ዝፍት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው።
እንዲሁም ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፤ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ”(ዘፍ፲፩፥፫-፬) እንዲል በአንድነት ተሰብስበው ግንብ መሥራት ጀመሩ። ግንቡንም እየሠሩ ወደላይ በሄዱና በወጡ ጊዜ ልባቸው በእግዚአብሔር ታበየ ከመታበይም በላይ ሥላሴን መግደል አለብን ብለው ወደሰማይ ጦር መወርወር ጀመሩ ይላል። ጦሩንም ሰይጣን በምታት ደም እየቀባ ይልክላቸው ጀመር በዚህ ሰዓት አሁን አብን ወጋነው አሁን ወልድን ወጋነው አሁን መንፈስ ቅዱስን ወጋነው እያሉ በእግዚአብሔር ላይ መዘባበት ጀመሩ። እግዚአብሔርም ቢታገሣቸው አልመለስ ንስሐ አልጋባስላሉ
“እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ።
እግዚአብሔርም አለ። እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም።
ኑ፥ እንውረድ፤ አንዱ የአንዱን ነገር እንዳይሰማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።
እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፤ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ።
ስለዚህም ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና፤ ከዚያም እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ እነርሱን በተናቸው”(ዘፍ፲፩፥፭-፱) እንዲል አንዱ ያንዱን ቋንቋ እንዳይሰማና መሥራት እንዳይችሉ ሥራውም እንዳይቀጥል ሥላሴ ቋንቋቸውን ደባለቁባቸው። ቋንቋቸው ስለተደባለቀ አንዱ ያንዱን ቋንቋ መስማት ስላልቻለ ጭቃ ሲባል ድንጋይ(ጡብ) ፣ ድንጋይ(ጡብ) ሲባል ጭቃ እያመጡ ስላልተስማሙ መሥራት አቁመዋል። የተሠራውንም ሕንፃ ሥላሴ በነፋስ አፍርሰውታልና ይህን በማሰብ ጥር ሰባት ቀን በደመቀ መልኩ ይከበራል።
✔️አሁንም ብዙ የካብነው የኃጢአት ግንብ፣ የመለያየት ግንብ፣ የጥላቻ ግንብ ፣ የምንፍቅና ግንብ፣ የክህደት ግንብና ብዙ የገነባናቸው የመገዳደል ግንቦች አሉና ሊፈርሱ ያስፈልጋል።
ይሄ ካልሆነ ክፋት ከማድረግ ልናቆም አንችልም። እነ ናምሩድ መስራት ያቆሙ ግንቡ ስለፈረሰ ነው እኛም በሀገራችን የገነባነውን የመለያየት ፣ የጥላቻ ፣ የመገዳደል ግንብ በፍቅር አፍረሰን ልናቆም ይገባል።
እነሱ ግንቡን መሥራት ያቆሙ ሥላሴ ወርደው ግንቡን በነፋስ ስላፈረሱት ነው። አሁንም የገነባነውን ኃጢአት በንስሐ ፣ ጥላቻውን በፍቅር፣ መለያየቱን አንድ ሐሳብ በመሆን ፣ መገዳደሉን በመረዳዳት ነፋስ ልናፈርሰው ይገባል ።
የኃጢአት ግንብ መሥራት እግዚአብሔርን ያሳዝነዋል። በመለያየትም የምንጠቀመው ነገር የለም የባሰ ወደሞትና ሀገርን ወደማፍረስ መሄድ እንጂ። በጥላቻና በመለያየት የሚያድግና ያደገ ሀገር የለም ሀገር የሚያድገው በአንድነት በመፈቃቀር ነው እንጂ።
✔️በእውነት በሀገራችን ላይ የተሠራውን የመለያየት፣ የመጠላላት ፣ የመገዳደል ግንብ አፍርሶ የፍቅር የአንድነትን ግንብ እግዚአብሔር ይገንባልን። እኛም በሚሞት ሥጋችን የኃጢአት ግንብ ገንብተን በዚያ ተሸጉጠን ከመኖር እግዚአብሔር ያውጣን ብዙዎቻችን በዚህ የኃጢአት ግንብ ውስጥ ነው የምንኖር ስለሆነም ሥላሴ ይህን ግንብ አፍርሶ በልቡናችን ፍቅርን ይገንባልን!!!
 በመምህር ዳንኤል አለባቸው
ጥር፮ /፳፻፲፫

 
Share this

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *